Wednesday, May 16, 2012

ቅኝ የተገዛው ‹‹ የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ›› እና የወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ባንዳነት ሲፈተሽ


ከጠቅላይ ቤተክህነት ከሚወጡት የሕትመት ውጤቶች አንዱ የሆነው ይህ ጋዜጣ መታተም ከጀመረበት ከ 1948 ዓ/ም እስከ 1967 ዓ/ም ድረስ ተወዳጅና ለብዙ አንባቢያን ተደራሽ ነበር፡፡ከ 1967 ዓ/ም በኃላ ጋዜጣው የሚያነሳቸው ሀሳቦች አወዛጋቢና ያዘጋጁን የተለጣፊነት ባህሪ አጉልተው የሚያሳዩ፣ ግለሰብን ማወደሻ፣ ቤተክርስቲን ማርከሻ መድረክ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተነባቢነቱ ቀንሷል፡፡


      ለ37 ዓመት የጋዜጣው ባልደረባና አዘጋጅ በመሆን በሥራ ላይ ያሉት አቶ ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ለዚህ ጋዜጣ ውድቀት አቶ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔርን በማስከተል ይመራሉ፡፡ ለጊዜው የካሕሳይን አጀንዳ እናቆየውና ወልደሩፋኤል ላይ ትኩረት እናድርግ፡፡
የዜና ቤተክርስቲን ጋዜጣ 56ኛ ዓመት ቁጥር 126 ሚያዚያ/ግንቦት 2004 ዓ/ም እትም ላይ እኝሁ ከላይ የጠቅስናቸው ግለሰብ ‹‹ የአባቶች ገበና በሕገ-ቤተክርስቲያን ሲጋለጥ ›› በሚል  ያሰፈሩትን ርዕስ አንቀፅ መነሻ በማድረግ ሰውዬው ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ይልቅ ለጥቅምና በየዘመኑ ላሉ ‹‹መሳፍንታዊ›› ገዢ መደቦች መስሎ አዳሪ እንደሆነ በዚህ ጋዜጣ ላይ ከ 1969 ዓ.ም እስከ አሁን ያሰፈራቸውን መልዕክቶች እየነቀስን እንመለከታለን፡፡
 ጋዜጣው የተነሳበትን ዓላማ ስቶ (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እምነት ትምህርት ባሕል ታሪክ ) ይዞ የሚወጣ ስለነበር የይዘት ጉድለት ሲያመጣ አንባቢ አጣ ለዚህም ይመስላል ጋዜጣው በግዳጅ በየአጥቢያው ያሉ ካህናት ሳይወዱ በግድ ከደመወዛቸው እየተቆረጠ ጋዜጣቸውን እንዲገዙ የሚደረገው፡፡
      ጥቅምት 14 ቀን 1969 ዓ/ም የታተመው ጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ ‹‹ የነገይቱ ቤተክርስቲያን ›› ‹‹ትላንት የነበሩ የቤተክርስቲያን መሪዎች በቤተክርስቲያን ላይ ጥቁር ነጥብ ጥለው አልፈዋል›› ይላል፡፡
      አባቶቻችን ቋንቋንና ፆታን ሳይለዩ መሪዎቹንና ሕዝቡን በአንድነት ጠብቀው ስለኖሩ ነው ጥቁር ነጥብ ጥለው ያለፉት? የተዋሕዶ እምነትን ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ስላስፋፉ ነው ጥቁር ነጥብ ጥለው አልፈዋል ተባሉት? ገዳማትን፣ አድባራትን እንዲሁም የአብነት ትምህርት ሳይበረዝ ሳይከለስ ስለጠበቁ ይሆን እንዲህ የተባሉት?
      በዚያው ዓመት ግንቦት 14 ቀን 1969 ዓ/ም ‹‹ከግላዊነት ወደ ብሔራዊነት ›› በሚለው ርዕስ አንቀፅ ላይ ‹‹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ ተግባሯና ከብሔር አቀፍ ሓላፊነቷ ፈር ወጥታ የጥቂት የቆብ አምባገነኖች ስመ ካህናት የግል ንብረትና የስጋ ገበያ መቆየቷ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡›› በማለት ትችቱን ሲቀጥል ቤተክርስቲያን በዘመኑ የነበሩ የመኳንንትና የመሳፍንት ማዕድ ባራኪዎች በነበሩ ዘመኑ እንጦስና መቃርስ የቆብ ጥላ ተከልለው ሕዝቡን ስትበዘብዝ የኖረች ናት፡፡ ሲል በራሷ ጋዜጣ ቤተክርስቲያኗን ይወነጅላል፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ የደርግ መንግሰት ታላላቅ ገዳማትንና አድባራትን ወደ ሙዚምነት ለመለወጥ የቃጣበት ስለነበር ወልደፉፋኤል የቤተክርስቲያኗን ብሔራዊ ሀብትነት ረስቶ የመንግስት አጀንዳ የደጋፊ ሆኖ ብቅ አለ፡፡
      ይህ ግለሰብ ክፉ ክፉውን ካላሰበ እንቅልፍ አይወስደውምና ነሐሴ 21 ቀን 1970 ዓ.ም ‹‹ብቸኛው ፓትሪያርክ›› በሚል ርዕስ አንቀፅ ላይ ‹‹የመኳንንቱንና የመሳፍንቱን ትዝታ በሠራ ህዋሳቸው ተሰራጭቶ (በአጥንታቸውና በደማቸው ተገንብቶ) ያለ መቃብር ከማይለቃቸው ከኢዲዩ አባነፍሶች ጋር ስለሚሰሩና የአስተዳደር መዋቅር ፈጽሞ ያልተመረተላትን በሌላ ዘይቤ ሥጋዊና መንፈሳዊ ጎን ተለይቶ ያልታወቀላትን ተንሰፋፊ ቤተክርስቲያን ከባዶ ሜዳ ስለተረከቡ በአሁኑ ጊዜ ፊውዳላዊ ጠባይ በሰፈነበት አስተዳደር ማዕበል ውስጥ ተውተው ይታያሉ››ሲል በተዋሕዶ ላይ ተነሳ ባንዳ መሆኑንን ገልጾልናል፡፡
ጥቅምት 1 ቀን 1971 ዓ.ም ‹‹ የሚደግፍ ርምጃ በሚል ርዕስ አንቀጽ ደግሞ ቀይ ሽብር መፋፋምና የጳጳሳትን በጡረታ መውጣት በይፋ ደግፏል፡፡
      በዚሁ በጠቀስነው ወር 27 ቀን 1971 ዓ.ም ‹‹ ሰሞኑ ቤተክነት ውዥንበር ›› በሚል ርዕስ ደግሞ ግሩም ሆነ ሃሳብ አንጸባርቆ ነበር፡፡ እንዲህ ይነበባል፡፡
      ‹‹ በመሠረቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲባል የቤተክርስቲያን ሕልውና ማስከበሪያ እንጂ ግል ሰዎች ዕድሜ ቀጥል ጉባኤና ጥቅም ማስረከቢያ ክበብ አይደለም›› ብሎ ነበር፡፡ የዛሬ ሠላሳ ሦስት ዓመት፡፡
    ግና ምን ያደርጋል የማታ ማታ ‹‹ ክፉ ልማድ ያሰረቃ ከማዕድ ነውና ተረቱ በራሱ ላይ ተፈጸመ፡፡ የዚህ ሰው የበዛ ንዋይ/ገንዘብ/ አፍቃሪነት እና አሻጥረኝበት በተደጋጋሚ ሲያነሱ የነበሩ አባቶችም ‹‹ እባብ ቆዳውን እንጂ ባሕሪውን አይለውጥም ›› አሁን ያደረገው ያንኑ እኩይ ባሕሪ ነው ይላሉ፡፡ወልደ ሩፋኤልም ራሱ እንዳረጋገጠው ‹‹ የአሜሪካ ኦ/ተ/ቤ/ክን የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ባለ ሙሉ ስልጣን ዋና ኃላፊ ›› ኃይለጊዮርጊስ ጥላሁን አድራሽነት የዶላር ጉርሻ እንዳገኘ አልካደም፡፡ በጋዜጣ ላይ የወጣውም ጽሑፍ በአቡነ ፋኑኤልና በኃይለጊዮርጊስ የተቀናበረ ሲሆን ‹‹ኃይለ ጊዮርጊስ ካመጣው ዶላር ከንፈሬን ቀባባኝ››ሲል እኔም የቤተክርስቲያን ወዝ ሰጥቼ ርዕሰ አንቀጽ አደረኩት ብሏል፡፡
      እነዚህ ከላይ ለማሳየት ጠቀስናቸው ርዕስ አንቀጾች የተነሳነበት አጀንዳ በስሱ ቢያስረዱ እንጂ በዚህ ጽሑፍ በሰፊው የጠቀስኳቸውን ሌሎች አንኳር ርዕሶችን በጋዜጣው ላይ በሰፊው ታገኛላችሁ፡፡ ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና በተደጋጋሚ የጡመራ መድረክና ሌሎች የሃሰብ መለዋወጫ መድረኮች ላይ እንደሚባለው አስኳሉ የተሐድሶ ህዋስ ምንያህል አደጋ ለማድረስ በቤተክርስቲያኗ ንዋይ ላይ ዘረፋ እያደረሰ እንደሆነ እና ከዚህ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተላለፈባቸው ጉዳዮች እንደተዳፈኑ ሌሎች በስሌት የተቀመሩ አጀንዳዎችን በስርዋጽ በማስገባት አጀንዳ ማስቀየሪያና ጊዜ መፍጃ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ እንደ ወልደሩፋኤል ፈታሒ ያሉ አጋር የጥፋት መልክተኞች ቀኝ እጅ ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሄር የተባሉት ሰውም በዚህ የተሐድሶ ሕዋስ የገንዘብ ድጋፍ ለሕትመት ዝግጁ የሆኑ የተጣረሱ አስተምሕሮዎችን የያዘ ሥራ እንዳዘጋጁ ይህ ጦማሪ ያውቃል፡፡
      የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ የይዘትና የተነሳበትን ዓላማ እንዳያስፈጽም ‹‹በድሮው እና ብቻ በእኛው ብቻ ይቀጥላል ›› ባዮችን እንዳሉበት ጥቅምት 2004 ዓ.ም በልዑልሰገድ ግርማ የጠ/ቤ/ክ/ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ቀርቦ የነበረው የመንበረ ፓትሪያርክ ጠ/ጽ/ቤት አስተዳዳሪው እና መዋቅራዊ ችግሮች የተሰኘ የዳሰሳ ምልከታ ላይ ተጠቁሟል፡፡
      በመሆኑም ቅዲስ ሲኖዶስ እንዳለው ወልደሩፋኤል ያቃለለውን የሰደበው መንፈስ ቅዱስን ስለሆነ ቀርቦ እንዲጠየቅ መደረጉ የብጹዓን አባቶችን ልበሰፊነትና አርቆ አሳቢነት የሚገልጽ ጎሽ የሚያሰኝ ተግባር ነው ፡፡ ቢሆንም ግን ከዚህ በኃላ ነገሮች ተሸፍነውና የተወሰኑ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የሁላችንም የበተክርስቲያን ልጆች ኃላፊነት ነው፡፡
      ቤተክርስቲያናችን በቅንቅን ተበልታ በመዥገር ተመጣ አጽሟ ብቻ ነው የቀረው በመሆኑም ከእኛ የሚጠበቀው የቤተክርስቲያን ተቋርቋሪነት መቼም የትም ብንሆን ቸል አንበል ሃሳባችንንም  በአንድነት ወደ ሥራ እንቀይረው ቀሪውን መንፈስ ቅዱስ ያከናውነዋል፡፡      

No comments: