እንግዳ ባልሆንባቸው የኢሕአዴግ አምባገነነናዊ አገዛዝ ሥር ላለፉት ሃያ ዓመታት የተለያዩ የግፍና የጭቆና ሕይወትን አሳልፈናል ፤ ዕድሜና ጤናዉን ይስጠን እንጂ ገና ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ደግሞ‹‹ እንዲህ እንዲህ እያልን አብረን እንዘልቃለን፡፡››(ይህን ቃል ከኢትዮጵያ ሬድዮ የተዋስኩ ሲሆን ባለማስፈቀዴ በኮፒ ራይት መብት ጥሰት እንደማልቀጣ ተስፋ አለኝ ፡፡) አንተ ማን ነህና ነው የማትቀጣው እንደምትሉኝ ልመንና መልስ ልስጥ፡፡
በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ የሰማናቸው ዜናዎች የሁሉንም ጆሮና አይን ቀጥ እንዲል ያደረጉ ናቸው፡፡የጋሽ ስብሃት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር ሞትና እና በአቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ የተቃጣው ድብደባ በፖለቲካው ጎራና ከዚህ ጽንፍ ርቀው ያሉትን ኢትዮጵያውን አንድ መንፈስ የደመረ የሃዘን ቀናት ናቸው፡፡የሚፈልገውን ሆኖና አድርጎ ያለፈው ጋሽ ስብሃት ጽፎልን ባነበብናቸው መጻሕቶቹ ስቀን፤ተቆጥተን፤አንዳንዴም ባሕላችን አረከሰው ብለን አንጃ ለይተን ተከራክረን አልፈናል፡፡ጋሼም ዶማን ዶማ እንጂ ማሻሻያ ቋንቋ እየፈለጉ እውነትን መደበቅ እንደማይኖርብን ሞግቶ ጽሁፉን እንደወረደ አሳትሞታል፡፡ነፍስ ይማር፡፡
ሌላው ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ የዕድሜ ልክ እስረኛ በሆነ ‹‹ታራሚ›› የደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ለሕይወቱ አስጊ መሆኑን፤ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ ስጋት እንደገባው፤መንግስትም ሆነ ብሎ እውነት በዱላ ለማፈን እያደረገ ካለው እንቅስቃሴዎች አንዱ ማሳያ ነው፡፡አንዱአለም በሚያራምደው ፖለቲካዊ አቋም እየደረሰበት ያለው ድብደባ ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን ከ1997 ዓ.ም እስከ ታሰረበት ጊዜ የተለያዩ ክትትሎች፤ ዛቻና ማስፈራራት ሲደርስበት ቆይቷል፡፡ይህ በአንዱዓለምና በሌሎች የፖለቲካ አጋሮቹ ላይ የተቃጣው የውንብድና ሥራ የወያኔ የ37 ዓመታት መክሊታዊ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ለዘመናት እንዳየነውና ከመጻሕፍት እንዳነበብነው አምባነናዊ መንግስታት ሲያልፉ ሃገርና እውነት ግን ቋሚ ናቸው፡፡እውነት በዱላ የምትሸፈን ሳትሆን እያደር እየፈካች የምትሄድ ቀይ ኮከብ ነች፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡